| አትሌቲክስ| እግር ኳስአትሌቲክስእግርኳስዜና

የአደይ አበባ ስታዲየም የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 99.7% ተጠናቀቀ

ከተጀመረ 4 ዓመታትን ያስቆጠረው ብሄራዊ ስታድየሙ ዛሬ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ መርሃግብር ጉብኝት ተካሂዷል። በጉብኝቱም ወቅት በመጀመርያ ምዕራፍ የተጠናቀቁ ስራዎች በአማካሪ ድርጅቱ ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ በኩል የተለያዩ ገለፃዎች ተደርጓል።

በአጠቃላይ 48 ሄክታር ላይ ያረፈው ስታዲየም የመጀመሪያ ምዕራፉን ለማጠናቀቅ 2.47 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል። አደይ አበባ ስታዲየም በወንበር 60000 ተመልካች መያዝ የሚችል ሲሆን ለ 2000 ቪአይፒ የሚሆን ሰፍራ ተዘጋጅቷል።

በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ውስጥ ከተካተቱት ውስጥም ከ 110000 ሜትሪክ ቶን በላይ የኮንክሪት ሙሌት ስራ ፣የፍሳሽ ማስወገጃ ፣ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ፣ከ30 በላይ የሚዲያ ክፍሎች፣ጋዜጣዊ መግለጫ አዳራሾች፣ የተለያዩ ደረጃውቸውን የጠበቁ ላውንጆች እና ከ1000 በላይ መፀደጃ ክፍሎች ተጠናቀዋል። ስታዲየሙ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከ3500 በላይ የመኪና ማቆሚያ፣ 3500 ተመልካች የሚይዝ መለስተኛ ስታዲየም የመረብ ኳስ የእጅ ኳስ የመሷሰሉትን የስፓርት ማዘውተሪያዎችን የሚይዝ ሲሆን ሰው ሰራሽ ወንዝም እንደሚኖረው በማብራሪያው ወቅት ተጠቅሷል።

2ኛውን ምዕራፍ ለማጠናቀቅ 900 ቀናትን የሚፈጅ ሲሆን ይህንንም ለማከናወን ጨረታ መርሃ ግብርም ተጠናቆ አሸናፊውም ተለይቶ ወደ ውል የስምምነት ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ከጉብኝቱ መጠናቀቅ በኋላ ማብራሪያ የሰጡት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ባህል እና ስፓርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ተናግረዋል ለ2ኛው ምዕራፍ 2.4 ቢሊየን ብር መንግስት በዚህ አመት በጀት እንደያዘለትም ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልፀዋል። በ2ኛው ምዕራፍ የጣራ ማልበስ፣የተመልካች ወንበር ፣የመጫወቻ ሜዳ ሳር ተከላ እና እንክብካቤ ፣የመሮጫ ትራክ የመሳሰሉት ወሳኝ ስራዎች ይከናወናሉ።

በተያዘለት መርሃ ግብር ቀሪው ግንባታውን ማካሄድ ከተቻለ ስታዲየሙ በ2014ዓ.ም መጨረሻ ይጠናቀቃል።

Similar Posts