አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከረዥም ዓመታት በኋላ በዓለም ሻምፒዮና ላይ በማራቶን ዳግም ነገሱ

ዛሬ መስከረም 24 ለእኩለ ሌሊት 1 ደቂቃ ሲቀረው የጀመረው የዶሃ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ተጠናቀቀ፡፡

ውድድሩን ሌሊሳ ዴሲሳ 2፡10፡40 በሆነ ሰዓት 1ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሞስነት ገረመው 02፡10፡44 በሆነ ሰዓት ሌሊሳን ተከትሎ በሁለተኝነት ውድድሩን ፈፅሟል፡፡

በዶሃ ያለው አየር በጎዳና ላይ እንደልብ ለመሮጥ አዳጋች ቢሆንም ሌሊሳ እና ሞስነት ብርቱ ትግል በማድረግ ከ18 አመታት በኋላ የዓለም የማራቶን ሻምፒዮና ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ በማድረግ ትልቅ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ በውጤቱም መሰረት ለሀገራቸው ወርቅ እና ብር አስገኝተዋል፡፡ በማራቶኑ የተሳተፈው ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሙሌ ዋሲሁን ውድድሩን ሳይጨርስ ቀርቷል፡፡

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ወርቅ ያገኘችው በአትሌት ገዛኸኝ አበራ አማካኝነት እ.ኤ.አ በ2001 በኤድመንተኑ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

Similar Posts