አትሌቲክስ

የዶሃ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጀመሪያ ቀን ውሎ

መስከረም 17/2012 ዓ.ም – በኳታር ዶሃ በተጀመረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና በተደረጉ የማጣሪ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለግማሽ ፍፅሜ እና ፍፃሜ ማለፍ ሲችሉ በሴቶች ማራቶን ተሳታፊ የነበሩት 3 አትሌቶች ውድድራቸውን አቋርጠዋል።

በሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ማጣሪያዋን ያደረገችው ደርቤ ወልተጂ ከምድብ አራት 02፡02.71 5ኛ ደረጃን በመያዝ ብታጠናቅቅም ያስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት ዛሬ ለሚከናውነው ግማሽ ፍፃሜ እንድታልፍ አስችሏታል።

በ3000ሜ መሰናክል ማጣሪያ መቅደስ አበበ ፣ሎሚ ሙለታ እና ዘርፌ ወንድማገኝ የተሳተፉ ሲሆን መቅደስ አበበ ከምድብ 1 በ9:27.61 4ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ፍፃሜ ስታልፍ፣ ከ ምድብ 2 ሎሚ ሙለታ በ 9:49.28 10ኛ እንዲሁም ከምድብ 3 ዘርፌ ወንድማገኝ በ9:43.75 7ኛ ደረጃን በመያዛቸው ወደ ፍፃሜ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ5000ሜ ማጣሪያ ከምድብ 1 ሰለሞን ባረጋ በ 13:24.69 ፣ ሙክታር እድሪስ በ13:25.00 1ኛ እና 3ኛ ደረጃን በመያዝ ሲያልፉ ከምድብ 2 ጥላሁን ወልዴ በ 13:20.45 የማጣሪይውን 2ኛ ሰዓት በማስመዝገብ በተመሳሳይ ለፍፃሜ አልፏል። ከዚሁ ምድብ አባዲ ሀዲስ 14ኛ ደረጃን በመያዝ ለፍፃሜ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።

ሰለሞን ባረጋ ሲያሟሙቁ እና በውድድር ወቅት የነበረው አየር ለውጥ ትንሽ እንዳስቸገረው ገልፆ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን በፍፃሜው ጥሩ ውጤት እንደሚያመጡ ሲገልፅ ሙክታር እድሪስ በበኩሉ ወበቁ እንዳስቸገርው አስተያየቱን ሰጥቷል።

ከብዙ ውዝግብ በኋላ የተካሄደው የሴቶች ማራቶን 3ቱም ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ግማሽ ያህል የውድድር እንኳን ማድረግ ሳይችሉ አቋርጠው ወጥተዋል።

በውድድሩ ከተሳተፉት 68 አትሌቶች 28ቱ ውድድራቸውን ያቋረጡ ሲሆን የሻምፒዮናውም የምንግዜም ዝቅተኛው ሰዓት የተመዘገበበት ሆኖ አልፏል። በውድድሩ ኬንያውያዋ ሩት ቼፔንጌቲች በ 2:32:43 በሆነ ሰዓት 1ኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ለሃገሯ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች፡፡ ሩት ያስመዘገበችው ሰዓት ከግል ምርጥ ሰዓቷ በ15 ደቂቃ የዘገየ ሆኖ ተመዝግቧል።

Similar Posts