አትሌቲክስ

የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ምሽት በይፋ ይጀምራል

17ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ምሽት በይፋ የሚጀምር ሲሆን ኢትዮጵያ በሴቶች ማራቶን የውድድሩን የመጀመሪያ ሜዳልያ ለማግኘት ትፎካከራለች።

ዶሃ ኳታር – መስከረም 16/2012 ዓ.ም – 17ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዶሃ፡ ኳታር ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት ይከናወናል፡፡ በብዙ መንገድ ከፍተኛ መሻሻሎች እንደታየበት በተነገረው የዘንድሮው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ እንደሆነ የተመሰከረለት የተሳታፊ አትሌቶች ብዛት (2000)፣ ከ160 በላይ ሀገራት የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እና እስከ አንድ ቢሊዮን የሚደርስ የቴሌቪዥን ተከታታይ እንደሚኖረውም ይገመታል፡፡

በዚህ ውድድር የስደተኞች እና በገለልተኛ ማንነት የሚፎካከሩትን የሩሲያ አትሌቶች ሳይጨምር 208 ሀገራት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከተሳትፎ ባለፈ ለውጤታማነት ከሚጠበቁት ሀገራት ተርታ በመሆን ወደ ዶሃ አምርታለች፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ባረፈበት ኤዝዳን ሆቴል ዛሬ ማለዳ የቴክኒክ ውይይት ያከናወነ ሲሆን፡ በውይይቱ ወቅት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ልዩልዩ ባለሞያዎች ስለውድድሩ እና መሰል ጉዳዮች ቴክኒካዊ ማብራሪያ እና የከዚህ ቀደም የውድድር ልምዳቸውን ለተወዳዳሪ አትሌቶች አካፍለዋል፡፡

በመጀመሪያው ቀን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ውሎ ኢትዮጵያውን አትሌቶች በአራት ውድድሮች የሚካፈሉ ይሆናል፡፡

800ሜ ሴቶች ማጣሪያ፡ ተሳታፊ አትሌት- ድርቤ ወልተጂ ፡ የወድድር ሰዓት ከቀኑ 11፡10
የአለም የታዳጊዎች ውድድር የርቀቱ ባለድል እና የአፍሪካ ወጣቶች የ1500ሜ አሸናፊዋ ድርቤ ወልተጂ፡ ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሲሜንያን ጨምሮ ሌሎቹ የርቀቱ የከዚህ ቀደም አሸናፊ አትሌቶች በሆርሞን መጠን አለመስተካከል ምክንያት በማይወዳደሩበት ፉክክር በአዋቂዎች ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሯ አንዳች ውጤት ለማስመዝገብ ማጣሪያዋን የምታከናውን ይሆናል፡፡

3000ሜ መሰናክል ሴቶች ማጣሪያ ፡ ተሳታፊ አትሌቶች – መቅደስ አበበ፣ ሎሚ ሙለታ፣ ዘርፌ ወንድማገኝ – የውድድር ሰዓት – ምሽት 1፡00
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደሀገር ውጤታማ እየሆንን ከመጣንባቸው የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው በዚህ የውድድር ዘርፍ ላይ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በተለያዩ ውድድሮች ላይ በተከታታይ ጥሩ ውጤት ባመጡ ወጣት አትሌቶች በመወከሏ የስፖርቱ ቤተሰብ ከዚህ ውድድር በዘንድሮው ሻምፒዮና አንዳች የተለዬ ነገር እንዲጠብቅ አድርጎታል፡፡

5000ሜ ወንዶች ማጣሪያ፡ ተሳታፊ አትሌቶች – ሙክታር ኢድሪስ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ጥላሁን ሀይሌ፣ አባዲ ሀዲስ – የውድድር ሰዓት – ምሽት 1፡55
ኢትዮጵያውያን አብዝተው ድል እንደሚያስመዘግቡበት በሚጠብቁት እናብዙዎቹም የማሸነፍ ቅድመ ግምቱን ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሰጡበት የ5000ሜ ውድድር፡ ከላይ በስም የተገለጹት ውጤታማ እና በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙት ሯጮች ለሰኞ ምሽቱ ፍጻሜ ለማለፍ የማጣሪያ ውድድራቸውን ዛሬ ምሽት ያደርጋሉ፡፡

ማራቶን – ሴቶች – ተሳታፊ አትሌቶች – ሮዛ ደረጄ፣ ሩቲ አጋ፣ ሹሬ ደምሴ – የውድድር ሰዓት – ሌሊት 5፡59
በዶሃ ባለው አስቸጋሪ የሙቀት ሁኔታ ምክንያት ሰሞኑን ከነ አካቴው ሊሰረዝ እንደሚችል ሲነገር የቆየው የሴቶች ማራቶን ውድደር፡ የዘንድሮው የአለም ሻምፒዮና የመጀመሪያው የሜዳሊያ ውድድር እንደሚሆን እና አስቀድሞ በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት እንደሚከናወን አለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አስታውቋል፡፡

Similar Posts