እግርኳስ

ለሴካፋ ከ15 አመት በታች ውድድር የኢትዮጵያ ልኡክ ወደ ስፍራው ያመራል

በአስመራ ለሚካሄደው የሴካፋ ከ15 አመት በታች ውድድር የኢትዮጵያ ልኡክ ነገ ወደ ስፍራው ያመራል

በኤርትራ አስመራ ለሚደረገው የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ከ15 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን 20 ተጨዋቾችን ይዞ ይጏዛል::
ብሄራዊ ቡድኑን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከሴካፋ ጥሪው የቀረበው ሰኔ ላይ ቢሆንም ከአስተናጋጁ አስቀድሞ ማረጋገጫ ባለመገኘቱ ለዝግጅት አጭር ጊዜ እንዲኖ አድርጏል ተብሏል::

ብሄራዊ ቡድኑን የሚወክሉትን ተጨዋቾች ለመምረጥ ከኮካ ኮላ ውድድር ቢታሰብም ከእድሜ በላይ በመሆናቸው ሌላ አማራጭ ለመመልከት ተችሏል::
በዚህም በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ ከ400 በላይ ታዳጊዎች ተሞክረዋል::
የፌደሬሽኑ የቴክኒክ ልማት ዳይሬክተሩ አቶ መኮንን ኩሩ እንደገለፁት ከአድካሚው የምልመላ ሂደት በሗላ 92ቱ ታዳጊዎችን በመያዝ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የመጨረሻዎቹን የመለየት ስራ ተሰርቷል ብለዋል::

በሃገሪቱ ከ15 አመት በታች ውድድር ባለመኖሩ ተቸግረን ነበር ያሉት አቶ መኮንን አስልጣኞችን የመረጥነው ከአካዳሚዎች ነው ብለዋል:: ሰለሞን መልካ ከወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንዲሁም ሰለሞን ገለታ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በአሰልጣኝነት ተመርጠዋል::

ዋና አሰልጣኙ ሰለሞን መልካ ሶስት ጊዜ ብቻ ልምምድ አድርገው ወደ አስመራ እንደሚሄዱ የገለፁ ሲሆን እርስ በርስ የመግባባት ስራ ብቻ በታዳጊዎቹ ላይ ሰርተናል ብለዋል::ውድድሩም ልምድ የሚያገኙበት እንደሚሆን ጠቁመዋል::

ከሁለት አስርት አመታት በሗላ ለመጀመሪያ ጊዜ በእግር ኳሱ ወደ ኤርትራ የሚሄደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሁለቱ ሀገራት ሰላም መፍጠርን ተከትሎ ወደ ሁለተኛ ቤታችን የምንሄድ ያህል በመቁጠር ደስተኞች ነን ብለዋል::
በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉት ታዳጊዎች ከትጥቅ ጋር በተያያዘ ምንም ችግር እንደማይገጥማቸው የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም ወደ አካዳሚዎች የሚገቡበት ሁኔታ ይመቻቻል ተብሏል::
ኢትዮጵያ በመድረኩ ሁለተኛው ምድብ ላይ ስትደለደል ከዩጋንዳ ታንዛኒያ ደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ ጋር ትጫዎታለች::

Similar Posts