አትሌቲክስ

በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አሸኛኘት ተደረገለት ።

ስሞሮኮ ራባት ለሚደረገው ውድድር የአሸኛነት ፕሮግራሙ በሂልተን ሆቴል ሲደረግ የኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እርስቱ ይርዳ ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕረዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊወርጊስ እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ፕረዚዳንት ሱፐር ኢንቴደንት ደራርቱ ቱሉ በፕሮግራሙ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል::

12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታ ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ መልኩ ጊዜ ተወስዶ ዝግጅት እንደተደረገበት ሲጠቆም አትሌቶች የተሻለ የቴክኒክ ፣ የታክቲክ እና ስነ ልቦና ዝግጅት ያደረጉበት ፤ አሠልጣኞች በቂ ጊዜ ወስደው ሠልጣኞችን ለማብቃት እና ውጤታማ ለማድረግ ተግተው የሰሩበት ከመሆኑም ባሻገር ስፖርታዊ ተሳትፎአችን የጨመረበት ነው ተብሏል::

የቡድን መንፈስን በማጠንከር ፣ ኢትዮጵያዊ ዲሲፕሊን ጠብቃችሁ ፣ በብቃት እና በውጤት የተሻላችሁ በመሆን ሀገራችን በአፍሪካ መድረክ ደምቃ እና ሰንደቋ ከፍ ብሎ የሚታይበት ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ርስቱ ይርዳ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕረዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊወርጊስ በበኩላቸው በቆይታችሁ በኢትዮጵያዊ ስነመግባር እና በአስተማሪነት መሪ በመሆን ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ህዝቡ የሚጠብቀውን ውጤት በማስመዝገብ ተልዕኳችሁን አሳክታችሁ ልትመለሱ ይገባል ብለዋል ።

በውድድሩ ላይ መልካም ውጤት ለማምጣት ኮሚሽኑ እና ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጓል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተ/ም /ፕረዚዳንት ሱፐር ኢንቴደንት ደራርቱ ቱሉ በትልቁ መድረክ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት ሊሆን ይገባል ስትል ለተሳታፊዎቹ መልእክቷን አስተላልፋለች::

የተሳፊ ልዑካን ቡድን አባላት ተወካዮች በውድድሩ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን በመድረኩ ገልፀዋል ።

ከነሐሴ 13 ጀምሮ በሞሮኮ ራባት በሚካሄደው 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያ በ13 የስፖርት ዓይነቶች የምትሳተፍ ሲሆን ቼዝ ፣ ካራቴ እና 3 በ 3 ቅርጫት ኳስ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዯጵያ የምትሳተፍበት የስፖርት ዓይነቶች ናቸው ።

ኢትዮጵያ ባለፋት 11 የአፍሪካ ጨዋታዎች በተሳተፈችባቸው ስፖርቶች 39 ወርቅ 49 ብር እና 63 ነሃስ በድምሩ 151 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች::

ግብፅ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ በርካታ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሲመሩ ኢትዮጵያ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች::

Similar Posts