እግርኳስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን አሸንፏል

ባለፈው ሳምንት ድሬደዋን 1ለ0 ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ጋር አቻ የተለያየው ደደቢትን አስተናግዷል። በውጤቱ ባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ0  ሲያሸንፍ ሰላሃዲን ሰኢድ እና አቤል ያለው ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፈው ጨዋታው  አሰላለፍ ውስጥ አቡበከር ሳኒን በበኃይሉ አሰፋ ተክቶ ተጠቅሟል፣ በደደቢት በኩል ደግሞ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ ተደርጓል።

በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሙከራን ለማድረግ ቅዱስጊዮርጊስ ቀዳሚው ነበር በሶስተኛው ደቂቃ በበሀይሉ አሰፋ አማካኝነት፣ ከቆይታዎች በኃላ ደግሞ ከቅዱስጊዮርጊስ በኩል ተከላካዩ ሰላሃዲን ባርጊቾ በጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል፣ምንተስኖት አዳነ ተክቶት ገብቷል።

በ18ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ አስደንጋጭ ሙከራን አድርጓል፣ 21ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምአንተ ካሳ ላይ ፍሪምፖንግ አሞስ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የመሀል ዳኛው ቅጣት ምትን ከቢጫ ካርድ ጋር ሰጥተዋል፣ በውሳኔው የደደቢት ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ቅሬታቸውን ገልፀዋል። ከዚህ ክስተት ስድስት ደቂቃ በኃላ በደደቢት ግብ ክልል አቅራቢያ የተገኘውን ቅጣት ምት ሳለሃዲን ሰኢድ በቀጥታ መቶ አስቆጥሮታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በደደቢት በኩል ኢላማውን ያልጠበቀ አንድ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።

 በዚህ ውጤት ወደመልበሻ ቤት ያመሩት ቡድኖቹ ከእረፍት መልስ ሲቀጥሉም በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሪ የመሞከር ቅድሚያውን የወሰደው ጌታነህ ከበደ ነበር፣ ከዚህ በኃላ ጌታነህ ከበደን ቀይሮ የገባው አቤል ያለው ተቀይሮ እንደገባ ባገኘው የመጀመሪያ ኳሱ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ዓለምአንተ ካሳ በደደቢት በኩል ወደፊት ተጠግቶ የመታት ከረር ያለች ኳስ ተጠቃሽ ነበረች፣ በጨዋታው 87ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሙሉዓለም መስፍን አስደንጋጭ ሙከራን አድርጎ ሳጥን ውስጥ በቅርብ ርቀት የመታት ኳስ ወጥታበታለች። ከጨዋታው በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረናል የፈጠርነውን ዕድል አልጠቀምንም፣ ተመሳሳይ ስህተቶችን ነው ዳኞች ላይ እያየን ያለነው  አንድ ተጫዋች መውጣት ሲገባው ያ ባለመሆኑ ዳኝነቱ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል”  የደደቢቱ ዋና አሰልጣኝ ኤሊያስ ኢብራሂም

“በምንፈልገው መልኩ ተንቀሳቅሰናል ብዬ አላስብም፣ ጨዋታው 50/50 የሆነ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር፣ የገጠምነው በሊጉ እታች የነበረ ቡድን ቢሆንም ጨዋታው ቀላል አልነበረም፣ የምንፈልገውን ነጥብ ማግኘታችን አስደስቶኛል፣ ወደሊጉ አናት መምጣታችንም ትልቁ ነገር ነው፣ ከዚህ በላይ መሻሻል ይገባናል” የቅዱስ ጊዮርጊስ ስቴዋርት ጆንሃል

Similar Posts