እግርኳስ

ንግድ ባንክ እና አዳማ በነጥብ ልዩነታቸው ቀጥለዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዲቪዚዮን የዘጠነኛው ሳምንት አምስት  ጨዋታዎች  ዛሬ ተደርገዋል።

ተጠባቂ የነበረው እና ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል፣ አዲስ አበባ ስቴዲየም  ላይ በተደረገው  ይህ ጨዋታ አዳማ ካሸነፈ  መሪነቱን የሚረከብበት፣ ንግድ ባንክ ከረታ ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን የሚያሰፋበት ይሆን ነበር፣ ውጤቱ አቻ መሆኑን ተከትሎ  አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት ቡድኖች አሁንም ከነነጥብ ልዩነታቸው ቀጥለዋል።

አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3ለ0 አሸንፏል። ተከታታይ ድልን ያሳከው መከላከያ ነጥቡን ከፍ በማድረግ ደረጃውን በማሻሻል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፣ ውጤቱ ከሁለተኛው አዳማ ጋር እኩል እንዲሆን አድርጎታል።

ድሬደዋ ከተማ በሜዳው አዲስ አበባን 2ለ1 አሸንፏል። ወደ ባህርዳር ያመራው ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከጥረት ኮርፖሬት ጋር 1ለ1 ተለያይቷል፣ አርባምንጭ ከሀዋሳ ሌላኛው በተመሳሳይ ውጤት አቻ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው።

ጌዲኦ ዲላ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ለዛሬ ተይዞ ወደ ማክሰኞ የተቀየረ ሌላኛው የዘጠነኛ ሳምንት  መርሃ ግብር ነው።

ፕሪምየር ሊጉን ንግድባንክ በ23 ነጥብ እየመራው ይገኛል፣ አዳማ ከነማ እና መከላከያ ከመሪው በሁለት ነጥብ ዝቅ ብለው በእኩል ነጥብ ተከታታዩን ደረጃ ይዘዋል። ሀዋሳ እና ጌዲኦ ዲላም በተመሳሳይ 16 ነጥብ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

Similar Posts