እግርኳስ

ፌዴሬሽኑ እስከ ጥር 14 ቀነ ገደብ ሰጠ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ጥር 7/2011 የፕሪምየር ሊግ ካምፓኒ ምስረታን አስመልክቶ ከ ክለቦቹ ጋር ውይይት አድርጓል።

በቅርቡ ከ500 ገፅ በላይ የያዘውን የጥናት  ሰነድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፣ ከዚሁ ጥናት አንዱ ክፍል የሆነውን የሊግ አደጃጀት ጉዳይ እንደነበር ይታወቃል። የአደራጃጀት ጥናቱ ከሰነዱ ውስጥ 145 ገፅ እንደያዘ ተነግሯል።

ይህንንም የጥናት ክፍል በአቶ ገዛኸኝ ወልዴ አቅራቢነት እንዲቀርብ ተደርጎ በቀረበው ጥናት ላይ ክለቦቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በጥናቱ የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ ለማሳያነት እንደቀረበ የተነገረ ሲሆን ከቀረቡት አማራጮች መካከል፣ ፌዴሬሽኑ በተወሰነ መልኩ የሚኖርበት፣ እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ ክለቦች ባለቤት የሚሆኑበት ከቀረቡት አማራጮች መካከል ይገኛሉ።

ክለቦቹ የየራሳቸውን ተወካይ በመላክ መዋቅሩ እንደሚሰራ ተገልፇል።የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ “የማመቻቸት ስራውን እንሰራለን፣ የምትልኳቸው ተወካዮች ለሚሰሩት ስራም ቢሮ እንሰጣቸዋለን” ብለዋል።

በዛም መሰረት በእለቱ  ሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ስሁል ሽረ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩ.፣ ፋሲል ከነማ፣ ባህርዳር ከነማ እና ድሬደዋ ከነማ በዚሁ ቀን የሚወክላቸውን ሰው ፅፈው የሰጡ ሲሆን፣ በፕሬዝዳንቱ በኩል 16ቱም ክለቦች እስከ ጥር 14 ድረስ ይወክለኛል የሚትሉትን ባለሙያ በደብዳቤ ፅፈው እንዲያሳውቁ መልዕክት ተላልፏል።

ከስብሰባው መጀመር በፊት “የክለብ ፕሬዝዳንቶች እና አንድ ተጨማሪ ተወካይ ነው እንዲገኝ ደብዳቤ የፃፍነው፣ ውሳኔ የሚፈልግ ነገር ስለሆነ የክለብ ስራ አስኪያጆች እና ቡድን መሪ አላልንም ” የሚል ሀሳብ ከፌዴሬሽኑ በኩል ሲነሳ በክለቦቹ በኩል ደግሞ  “በህጋዊ መንገድ ውክልና የተሰጠን ሰዎች አለን” ፣ “በከተማ ቡድኖች በብዛት ፕሬዝዳንቶች ሌላም ተጨማሪ ሀላፊነት አላቸው ስለዚህ የተሻለ ቅርቡም እኛ ነን፣ ግን ሀሳብ ይዘን እየሄድን ውሳኔ ማስወሰን እንችላለን” የሚሉ እና ሌሎችም ምላሾች ተሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2012 ከማወዳደር ለመውጣት ዕቅድ እንዳለው በተደጋጋሚ ሲገለፅ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

Similar Posts