እግርኳስ

ጅማ አባ ጅፋር በአጋዴር  ተሸንፏል

በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ የነበረው ጅማ አባ ጅፋር በአል-አህሊ በደርሶ መልስ ውጤት መሸነፉን ተከትሎ ወደ ኮንፌዴሬሽን ውድድር አምርቷል።

በኮንፌዴሬሽኑ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውም ከሞሮኮው አጋዴር ጋር ያደረገውን ጨዋታ ተሸንፏል።

አዲስ አበባ ስቴዲየም ላይ የተደረገው ጨዋታ 1ለ0 ተጠናቋል። በሀዋሳ 3ለ1 ከተሸነፈበት ጨዋታ መልስ አዲስ አበባ ላይ ሲዘጋጅ የነበረው ጅማ አባጅፋር

አወት ገ/ሚካኤል፣ ዘሪሁን ታደለ፣ ኤልያስ አታሮ፣ እና ሄኖክ ገምቴሳ በጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች መሆናቸው ከጨዋታው በፊት ተነግሯል።

በጨዋታው ጅማሮ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ በዲዲዬ ሊብሬ አማካኝነት የተሞከረው ሙከራ ከጅምሩ ጎል ያስቆጥራል አስብሎለት ነበር፣ ኳሷ አንግሉን ገጭታ ተመልሳ ወጥታለች፣ በ9 እና በ29ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በአጋዴር በኩል አስደንጋጭ ሙከራ ተደርጎበታል። እረፍትን 0ለ0 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ አስቻለው ግርማ ሌላኛው ሞካሪ ተጫዋች ነበር። በጨዋታው 74ኛው ደቂቃ ላይ የአጋዴሩ ዞሂር ቾውች ጎል አስቆጥሯል። ከዚህች ግብ በኃላ በጅማአባጅፋር በኩል ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የተሞከረው ሙከራ ውጤቱን ለመቀየር የመጨረሻው አጋጣሚ ነበር።

ከጨዋታው በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የጅማ አባ ጅፋር ረዳት አሰልጣኝ ዩሱፍ ዓሊ

“የዛሬውን ጨዋታ እንደምታዩት የተሻልን ነበርን፣ 17 ልጆች ይዘን ነው የገባነው፣ በጉዳት ተጫዋቾች አልተሟሉልንም፣ ከእነሱ በጣም የተሻልን ነበርን፣ ሀይ ቦል ነው የሚጫወቱት፣ በዋናነት አብዛኞቹ የመስመር ተጫዋቾች ሁለቱ የሉም፣ በዚህች አጋጣሚ እንደዚህ አልጠበቅንም በየሶስት ቀኑ ስንጫወት ነበር፣ ተጠጋግተን እየተጫወትን፣ የጎል እድሎችን አልተጠቀምንም ነበር ፣ ወደቦክስ የመምጣት ዕድሉ ብዙ ባይሆንም ፣ አትጠራጠሩ ውጤቱን በመልሱ  ጨዋታ እንቀለብሰዋለን በውስጥ ህመም የታመሙብንን ተጫዋቾች በአራት ቀን ውስጥ እናገኛለን፣ እንቀለብሰዋለን”

የአጋዴር አሰልጣኝ  ሚጌል አንሄል ጋሞንዲ

“በውጤቱ ተደስቻለሁ፣ ስንመጣ አስቸጋሪ ጨዋታ እንደሚሆን አስበን ነበር፣ የጨዋታ ሜዳውም ለመጫወት ጥሩ አይደለም፣ አየሩም በሌላ በኩል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሶስት አራት የሚሆኑ ንፁህ ሙከራዎችን አድርገናል። ሞሮኮ ላይ ቀሪ 90 ደቂቃ እንጫወታለን ሜዳችንም ጥሩ ስለሆነ ተረጋግተን እንጫወታለን። ወደ ምድብ ድልድሉ መግባት ለክለቡ ልዩ ታሪክ ነው ፣ እግር ኳስ ስሜት አለው ተጫዋቾቹ ያን ስሜታቸውን ነው ያወጡት፣መሸነፍም ማሸነፍ አለው”

Similar Posts