እግርኳስ

ኢትዮጵያ ቡና መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ አንደኛው በአዲስ አበባ ስቴዲየም ኢትዮጵያ ቡናን ከ ስሁል ሽረ ያገናኘው ጨዋታ ይገኝበታል። ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ቡና ካለፈው ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጓል፣ አማኑኤል ዩሀንስን ፣እንዲሁም ሳምሶን ጥላሁን  በዚህ ቀን ያልነበሩ ተጫዋቾች ናቸው፣ ስሁል ሽረ መቀለን ከገጠመው ቡድናቸው ውስጥ የሶስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርጓል።

በጨዋታው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ አስደንጋጭ የሚባሉ ሙከራዎች ባይደረጉም፣ በ10ኛው ደቂቃ ላይ በ18 ካሉሻ አልሀሰን ሙከራዎችን አድርገዋል፣ ማድ ፎፋና በ20ኛው ደቂቃ ለስሁል ሽረ የመጀመሪያው ሞካሪ ነበር።

ጅላሉ ሻፊ በ25ኛው ደቂቃ ያደረጋት ሙከራም በስሁል ሽረ በኩል ተጠቃሿ የመጀመሪያው አጋማሽ ሙከራ ስትሆን፣ ከዚህ በኃላ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ካሉሽ በጭንቅላት ገጭቶ የወጣበት ኳስ ኢላማን በመጠበቅ የተሻለችዋ ኳስ ነበረች። ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ቤት ለማምራት ጭማሪ ደቂቃ ላይ እያሉ  የዕለቱ አርቢትር የስሁል ሽረው ክብሮም ብርሃነ በእጅ የነካት ኳስ ፍፁም ቅጣት ናት በማለታቸው የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ነስሩ ወደ ግብነት ቀይሯት ኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 መርቷል።

የስሁል ሽረ ቡድን አባላትም ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፣ ፍፁም ቅጣት ምቱ ከመመታቱም በፊት ግብ ጠባቂውን ጨምሮ ተጫዋቾቹ በአሰልጣኝ መቆሚያ (ቴክኒክ ቦታ) ጋር ተሰብስበው ታይተዋል። በዚህ ውጤትም ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ስሁል ሽረ በጅላሉ እና በሜዲ ፎፋና አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ግብ ክልል መቅረብ ቢችሉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ኢትዮጵያ ቡና በአቡበከር ነስሩ እና በተመስገን ካስትሮ ካደረጋቸው ሙከራዎች ውጪ በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም ወደግብ መቅረብ ሳይችል ቀርቷል። ብዛት ያላቸው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በቡድናቸው አቋም አሰልጣኙ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ከጨዋታው በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“የዕለቱን ጨዋታ እንድንሸነፍ ያደረገን ዳኛው ነው፣ውጤቱ አይገባንም ነበር፣ በሁለተኛው አጋማሽም ተጭነን አጥቅተን ተጭነን ተጫውተን ነበር፣ ዳኝነቱን ምክንያት ማድረግ አንፈልግም ነገር ግን ፍፁም ቅጣት ምቱን ረዳት ዳኛው ነበር ቅርቡ እሱ አይደለም ብሎ ዋናው ዳኛ ነው ብሏል። ይህ አሳዝኖናል። ተጫዋቾቹ ተረጋግተው እንዲጫወቱ እና ካርድም እንዳያዩ ነው ሰብስበን ስንመክር የነበረው፣ እንጂ ሜዳ ጥሎ የመውጣት ሀሳብ አልነበረንም” የስሁል ሽረው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ

“ጨዋታው ጥሩ አልነበረም፣ ቡድናችንም ጥሩ አልነበረም፣ ደጋፊዎቹን እረዳለሁ፣ብናሸንፍም በአቋማችን ደስተኛ አይደለሁም፣ በጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች አሉን፣ በቀጣይ ማሻሻል የሚገቡን ብዙ ነገሮች አሉን”  የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዲዲዬር ጎሜዝ

Similar Posts