እግርኳስ

አዳማ ከተማ በሰፊ ጎል ልዩነት መከላከያን አሸነፈ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ9ኛውን ሳምንት ከከፈቱ ሁለት ጨዋታዎች አንደኛው የሆነው መከላከያን ከአዳማ ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ የ5ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ዳዋ ሁቴሳ አራት ጎሎችን በማግባት ከፍተኛው ቁጥር ሲወስድ፣ በረከት ደስታ ሌላኛው የአዳማ ግብ አግቢ ነው። ለመከላከያ ብቸኛዋን ግብ ምንይሉ ወንድሙ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።

ሁለቱም ቡድኖች ያለግብ በቆዩባቸው የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በተቀራራቢ የጨዋታ ፍሰት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነበር፣ በአዳማ በኩል ቡልቻ ሹራ እና በረከት ደስታ በ11ኛው እና በ14ኛው ደቂቃዎች ያደረጉት ሙከራ እንዲሁም በመከላከያ ምንይሉ ወንድሙ በ15 ኛው ላይ ያደረገው ሙከራ ተጠቃሾች ናቸው።

በ21ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል አንደኛው የነበረው የአዳማው ከነዓን ማርክነህ ያሻገራትን ኳስ በረከት ደስታ ወደግብነት ቀይሮ አዳማን መሪ አድርጓል።

ከዚህች ግብ መቆጠር ብዙም ሳይቆይ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ  በእጅ የተነካ ኳስ በሚል አርቢትሩ ለመከላከያ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል፣ ምቷንም ምንይሉ ወንድሙ አስቆጥሮ 1ለ1 መሆን ችለዋል። ከዚህም በኃላ አዲስ ህንፃ በ27ኛው፣ ዳዋ ሁቴሳ በ39እና በ44ኛው አስደንጋጭ የሚባሉ ሙከራዎችን አድርገዋል፣ በዚህም ውጤት ወደ እረፍት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከ5 ደቂቃ በኃላ ዳዋ ሁቴሳ አዳማን ወደመሪነት ያሻገረችዋን ግብ አስቆጠረ፣ በ54ኛው ደቂቃ ላይ ጥፋት ተሰርቶበት የነበረው የመከላከያው አጥቂ  ተመስገን ገብረኪዳን ከፊሽካው መልስ በመሀል ራሱ በሰጠው ምላሽ በቀይ ካርድ ወጥቷል፣ ከዚህ ክስተት አምስት ደቂቃዎች በኃላም ወደግብ የምትሄድን ኳስ በእጁ የመለሰው ሌላኛው የመከላከያው ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች አለምነህ ግርማ ሁለተኛው በቀይ የወጣ ተጫዋች ሆኗል።

ይህን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሁቴሳ አስቆጥሯል፣ 69 እና 87 ሌሎች ተጨማሪ ጎሎችን ያስቆጠረው ዳዋ በተለይም ከበረከት ደስታ እና ከከነዓን ጋር የነበራቸው ተደጋጋሚ ቅብብል ብቻውን አራቱን ግቦች እንዲያስቆጥር ሚና ነበራቸው፣ ይህን ተከትሎም ተጫዋቹ  በሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 6 አድርሷል። ውጤቱ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አዳማን በ11 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጥ፣ ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት መከላከያ ደግሞ በ8 ነጥብ 11ኛው ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ከጨዋታው በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

“በሰፊ ጎል ማሸነፋችን ደስ ብሎኛል፣ ከነበረብን የውጤት ማጣት ለመውጣት የልጆቹ ጭንቅላት ላይ ነው የሰራነው፣ የቻላችሁትን አድርጉ ሀላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ ብያቸዋለሁ”  የአዳማው አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃ

“እርግጥ በዚህ ቀን ጥሩ አልነበርንም፣ ሁለት ተጫዋቾች መውጣተቸውም ሁኔታው ቀይሮታል፣ በራሳችን የውስጥ ደንብ የተጫዋቾችን ዲሲፒሊን ጉዳይ የሚታይ ነው የሚሆነው በቀጣይ ከዚህ ሁኔታ ውስጥ መውጣት ይኖርብናል።” የመከላከያው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ

Similar Posts