እግርኳስ

አቃቂ ቃሊቲ በመሪነቱ ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዲቪዚዮን  የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ረቡዕ እና ሀሙስ ተደርገዋል።

ረቡዕ አዲስ አበባ ስቴዲየም ላይ በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በመቀለ 70 እንደርታ 5ለ1 ተሸንፏል። የአሸናፊውን ቡድን ግቦች ዮርዳኖስ በርሄ(2)፣ ሰላም ተኸላይ፣ ርሻን ብርሃኑ እና አበባ ገ/መድህን ሲያስቆጥሩ ፣ ንፋስ ስልክን ያልታደገችዋን ግብ ማህሌት በቀለ አስቆጥራለች።

በእለተ ሀሙስ ሶስት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከነማ ከፋሲል ከነማ 0ለ0 ተለያይተዋል። አዲስ አበባ ስቴዲየም ላይ የዲቪዚዮኑ መሪ አቃቂ መሪነቱን ያጠናከበረትን ድል ቦሌ ክፍለ ከተማን 2ለ1 በማሸነፍ አሳክቷል።  ለአቃቂ ዙፋን ደፍርሽ እና ሰላማዊት ጎሳዬ ሲያስቆጥሩ፣ ሜሮን አበበ የቦሌን ብቸኛ ግብ አግብታለች።

ካለፈው ዓመቱ አንፃር አስከፊ የውጤት መንገድ ላይ የሚገኘው ልደታ በዚህ ቀንም ማሸነፍ አልቻለም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 1ለ0 ተሸንፏል፣ ለአሸናፊው ቂርቆስ ትሁን ፋሎ  አግቢዋ ናት።

አንደኛው ዙር ሊጠናቀቅ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እና የሰባተኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች የሚቀሩት ሲሆን፣
ዲቪዚዮኑን አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ  በ16 ነጥብ ሲመራ፣ መቀለ በ12 ይከተላል። ሻሸመኔ እና ቂርቆስ በ11 እና በ10 ነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል። ፋሲል ከነማ በ9 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሰባተኛው ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ ጥር 7 እንደሚደረጉ የወጣላቸው መርሃ ግብር ያሳያል።

Similar Posts