እግርኳስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታታይ አቻ መልስ አሸነፈ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ዛሬ የተደረገ ሲሆን ቅዱስጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር ያገናኘው ይህ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር በነበረበት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ምክንያት ቀድሞ በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት መካሄድ አልቻለም ነበር።

ጨዋታው በባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። 56ኛው በአቤል ያለው እንዲሁም በ61ኛው ደቂቃ በሰለሃዲን ሰዒድ አማካኝነት ግቦቹ ተቆጥረዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በ10 እና በ13ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ወደግብ በመሞከር ቀዳሚው ነበር፣ በጅማ አባ ጅፋር በኩል ተጠቃሹ ሙከራ በዲዲዬ ሊብሬ እና አዳማ ሲሴኮ ሞካሪዎቹ ነበሩ።

በ25ኛው ደቂቃ ከአጥቂዎች ተጠግቶ የተሰለፈው አቡበከር ሳኒ ለአቤል ያለው ያሻገራትን ኳስ በጅማ ተከላካዮች ወጥታለች። ሁለቱ ቡድኖች በ0ለ0 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ አስራ አንድ ደቂቃዎች በኋላ አቤል ያለው አንድ ለአንድ ከግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደግብ የላካት ኳስ ወደውጪ ወጥታበታለች፣ ከዚህች ኳስ ሁለት ደቂቃ በኋላ ነበር አቤል የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው።

61ኛው ደቂቃ ላይ ከአንድ ዓመት የጉዳት ቆይታ በኃላ ከሀዋሳ ጋር በነበራቸው ጨዋታ የተመለሰው ሰለሃዲን ሰኢድ ሁለተኛዋን ጎል አስገኝቷል።

ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ አልአህሊን 1ለ0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የመጀመሪያ የሊግ ግጥሚያውን ማድረጉ ነበር በሊጉም ሶስተኛው ጨዋታው ሲሆን በመክፈቻው አዳማን አሸንፎ በመሀከል ከሽረ ጋር አቻ ተለያይቷል አራት ተስተካካይ ጨዋታዎች አሉት፣በአራት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከሀዋሳ እና ከመቀለ ጋር በተከታታይ አቻ ከወጣ በኋላ ሶስት ነጥብ ያሳካው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ጋር ተስተካካይ ጨዋታ ሲኖረው በሁለት ጨዋታ አቻ ወጥቶ፣ ሁለቱን አሸንፎ በሁለቱ ደግሞ ተሸንፏል፣ በስምንት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በስምንተኛው ሳምንተ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም፣ ጅማ አባ ጅፋር በሜዳው ከወልዋሎ ጋር ይጫወታል።

Similar Posts