እግርኳስ

በተስተካካይ ጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ሶስት ነጥብ አሳካ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሶስተኛው ሳምንት ተስተካካይ አንድ ጨዋታ ዛሬ ተደርጓል። ኢትዮጵያ ቡናን ከወልዋሎ ያገናኘው ይህ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና የ1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በ60ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር በፍፁም ቅጣት ያስቆጠረው ግብ ተከታታይ ነጥቡን እንዲያሳካ አድርጎታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በወልዋሎ በኩል በ11ኛው እንዲሁም በ16ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ እና አፈወርቅ ሀይሉ አስደንጋጭ ያልሆኑ ሙከራዎችን አድርገው ነበር።

ካለፈው አሰላለፍ ሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ19እና 38ኛው ደቂቃ የተመስገን ካስትሮ የጭንቅላት ኳስ ሙከራ፣ በ28ኛው ደቂቃ የአቡበከር ናስር፣እንዲሁም የካሉሻ አልሀሰን የ33ኛው ላይ ተጠቃሽ ከነበሩት ሙከራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎች በደስታ ደሙ እና በኤፍሬም አሻሞ በኩል ሌላ ሙከራ ቢያደርጉም የተሳካላቸው አልነበረም።

ኢትዮጵያ ቡናዎችም በአህመድ ረሺድ እና ሚኪያስ መኮንን አማካኝነት ተጨማሪ ሙከራን አድርገዋል። ወልዋሎ ባለፈው ሳምንት ደደቢትን የረታ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ 1ለ0 ውጤት አዳማን አሸንፈው ነበር የተገናኙት።

ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ከዚህ በላይ ማሻሻል ያሉብን ነገሮች አሉ፣ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል እንዳለብኝ ይሰማኛል፣ የምንፈልገውን ነጥብ አግኝተናል፣ አዎ ከፊታችን ትልቅ ጨዋታ አለ፣ ከጨዋታ ጨዋታ ተመሳሳይ ዝግጅት እናደርጋለን በአዕምሮ ግን በደንብ መዘጋጀት እንዳለብን አምናለሁ።” የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዲዲዬር ጎሜዝ

“በጉዳይ ላይ ያሉብን ተጫዋቾች አሉ፣ አስራትም ያለፉትን 42 ቀናት ጉዳት ላይ ነበረ፣ ዋለልኝም በጉዳት የለም ይሄ ክፍተት ፈጥሮብናል፣ በሌላ በኩል የተሰጠብንን ፍፁም ቅጣት ምት አግባብ አልነበረም ግን በፀጋ ተቀብለናል።” ፀጋዬ ኪዳነማርያም

Similar Posts