እግርኳስ

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሃዋሳ ከተማ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣በስድስተኛው ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዋሳ ያደረጉት ይገኝበታል። ዕሁድ መደረግ ሲኖርበት በደጋፊዎች ፀብ ምክንያት ወደሰኞ የተሸጋገረው ይህ ጨዋታ 0ለ0 ተጠናቋል።

ባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፈው ጨዋታው ምንተስኖት አዳነን እና አሜ መሀመድን በጉዳት ምክንያት ሳይጠቀም ቀርቷል፣ በቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ጉዳት አጋጥሞት ቀዶጥገና አድርጎ የነበረው ሰለሃዲን ሰኢድ ወደሜዳ ተመልሶ ተቀይሮ ገብቶ ተጫውቷል።

በሀዋሳ በኩል የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት፣ የትላንቱን ሁኔታ ተከትሎ መንገድ ጀምረው እንደተመለሱ የተነገረው ሀዋሳ ከነማ አቻ መውጣቱን ተከትሎ የሊግ መሪነቱን አጠናክሮ ወደ 11 ነጥብ አድርጎለታል፣ ያለተመልካች የተካሄደው ጨዋታ ሳቢ እና ማራኪ እንቅስቃሴ ባይታይበትም አልፎ አልፎ የሚሞከሩ ሙከራዎች ነበሩት፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አቤል ያለው እንዲሁም በሀዋሳ እስራኤል እሸቱ ወደግቡ በመጠጋት ሙከራ ያደረጉ ተጫዋቾች ነበሩ።

ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

“ለማሸነፍ ሞክረናል፣ ተጋጣሚያችን ከመሸናነፉ ይልቅ የአቻ ውጤቱን መፈለጉ እኛ የተሻለ እንድንጫን አድርጓል፣ ደጋፊዎቻችንንም አጥተናል።
ሶስቱ አጥቂዎቻችን አሁን ከእኛ ጋር አይገኙም፣ ሰለሃዲን ከዓመት በኃላ ነው የተመለሰው ጊዜ ያስፈልገዋል፣ አሜ እና ጌታነህም ጉዳት ላይ ናቸው፣ በቀጣይ ጨዋታዎቻችን እናስተካክላለን፣ ስለተፈጠረው ሁኔታ ይህ አፍሪካ ነው፣በእግር ኳስ እንደሚፈጠር ይታወቃል።” የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ስቴዋርይ ጆንሃል

“በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ይህን ነጥብ ማግኘታችን አስደስቶናል፣ ከመንገድም እንደመግባታችን ጥሩ የሚባል ነው። ከእረፍት መልስ የተሻልን ነበርን፣ ከተጎዱብን ተጫዋቾች መካከል መሳይ ጳውሎስም አንደኛው ነው። የተፈጠረው ነገር አግባብ አልነበረም ቀዳሚው ሰላም ነው፣ ይህ ሁኔታ እንዲስተካከል በቀጣይም መታሰብ አለበት” የሀዋሳው አሰልጣኝ አዲሱ ካሳ

Similar Posts