እግርኳስ

በሴቶች ሁለተኛው ዲቪዚዮን አቃቂ መሪነቱን አጠናከረ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዲቪዚዮን የሶስተኛው ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ማክሰኞ በ9 እና በ11 ሰዓት ተደርገዋል።

ቀዳሚ በሆነው እና ልደታ ክፍለ ከተማን ከቦሌ ክፍለ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ 1ለ1 ተጠናቋል። ልደታ በመሪነት ለ78 ደቂቃዎች መቆየት ቢችልም በጨዋታ የመጠናቀቂያ ፊሽካ ሲጠበቅ ቦሌ አቻ መሆን ችሏል።

ሁለት ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዶ የነበረው ልደታ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ሳያሳካ ቀርቷል። ተጋጣሚው ቦሌ በተመሳሳይ አሸንፎ ባያውቅም ከሶስተኛ ሽንፈቱ ግን ማምለጥ ችሏል።

አቃቂ ክፍለ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶን በሰላም ሀይሌ ጎል 1ለ0 አሸንፏል። ሶስተኛ ጨዋታውን ያሸነፈው አቃቂ የሊግ መሪነቱን አጠናክሯል። ካለፈው ዓመት መልካም አጀማመሩ ላይም ይገኛል፣ ውጤቱን ተከትሎም ንፋስ ስልክ ደግሞ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሆኗል።

የዚሁ ሳምንት ጨዋታዎች ዕሁድ እለት መደረግ ሲጀምሩ ሻሸመኔ በሜዳው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 1ለ0 ተሸንፏል። ፋሲል ከነማ ከመቀለ የሚያደርጉት ጨዋታ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል። ዲቪዚዮኑን አቃቂ በ9 ነጥብ ሲመራ ቂርቆስ በ7 ይከተላል።

የዚሁ ዲቪዚዮን አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ ታህሳስ 9 ይደረጋሉ።

Similar Posts