እግርኳስ

አቃቂ እና ሻሸመኔ ተከታታይ ድል ሲያስመዘግቡ፣ ንፋስ ስልክ እና ልደታ ደግሞ በተቀራኒው ቆመዋል

አቃቂ እና ሻሸመኔ ተከታታይ ድል ሲያስመዘግቡ፣ ንፋስ ስልክ እና ልደታ ደግሞ በተቀራኒው ቆመዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዲቪዚዮን ሁለተኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል።

አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በተደረጉት በነዚህ ጨዋታዎች ቀዳሚው የነበረው ጨዋታ ንፋስ ስልክን ከሻሸመኔ አገናኝቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ እንግዳው ቡድን  ሻሸመኔ በዓለሚቱ ድሪባ በ14ኛ እና 23ኛ ደቂቃ በጨዋታ እንዲሁም በፍፁም ቅጣት ምት በተቆጠሩ ግቦች መሪነቱን በመያዝ ቀዳሚ ሆኗል፣ በዚህ ውጤትም ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ 65ኛው ደቂቃ ላይ ንፋስ ስልክ  በማርታ አያነው አማካኝነት ግብ አስቆጥሯል፣ ጨዋታው ቀጥሎም ከዚህች ግብ መቆጠር 10 ደቂቃ በኋላ ለሻሸመኔ ጡባ ነስሮ አስቆጥራ ጨዋታው 3ለ1 ላይ እንዲደርስ ሆኗል፣በመቀጠልም በንፋስ ስልክ በኩል ሁለተኛ ግብ ተቆጠረ፣ ትዕግስት ሽኩር ጎሉን ስታገባ ጨዋታው 85ኛው ደቂቃ ላይ ደርሶ ነበር።

በጨዋታው መጠናቀቂያ ሲቃረብ ግን ንፋስ ስልኮች “በእጅ የተነካ ኳስ አለ ፍፁም ቅጣት ምት አልተሰጠንም” በሚል ስሜት ቅሬታቸውን አሳይተዋል።

አቃቂ ክፍለ ከተማ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበበት ሁለተኛው ጨዋታ ጅማሮውን ያደረገው 11:10 ሲል ነበር።

ሊጉን መቐለን አሸንፎ በድል የጀመረው አቃቂ  በ47ኛ እና በ52ኛው ደቂቃ ላይ ሰላማዊት ሀይሌ ባስቆጠረቻቸው ግቦች ልደታን 2ለ0 አሸንፏል። አስቆጣሪያዋ ሰላማዊት ቀደም ሲል እቴጌ እና ንግድ ባንክ ተጫዋች ነበረች።
ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሻሸመኔ ተጉዞ ተሸንፎ የነበረው ልደታ ዛሬም ሁለተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
የዚሁ ዲቪዚዮን የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ሀሙስ እንዲሆኑ ቀን ወጥቶላቸዋል።
የአንደኛው ዲቪዚዮን ጨዋታዎች ግን ቅዳሜ እና እሁድ ይደረጋሉ።

Similar Posts