እግርኳስ

በሴቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ቂርቆስ እና አቃቂ ድል ቀናቸው

አቃቂ አዲሱ መቐለን ሲያሸንፍ፣ሁለት ጨዋታዎች ሳይደረጉ ቀርተዋል …በሴቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሁለት ዲቪዚዮን ተከፍሎ ይካሄዳል። በአንደኛው ዲቪዚዮን 12 ክለቦችን ሲያወዳድር በሁለተኛው ደግሞ 10 ክለቦች ይሳተፉበታል ተብሎ ነበር።

የሁለተኛው ዲቪዚዮን የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች መደረግ የጀመሩት ያሳለፍነው ዕሁድ የነበር ሲሆን ሻሸመኔ ከነማ ልደታ ክፍለ ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ 3ለ1 አሸንፏል። የዲቪዚዮኑ ቀጣይ ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ረቡዕ እንዲደረጉ ቀን ተይዞላቸው ነበር።

ማክሰኞ ዕለት ይደረጉ ከነበሩት ሁለቱ ጨዋታዎች አንደኛው ብቻ የተካሄደ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ንፋስልክ ክፍለ ከተማን 4ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር በዲቪዚዮን ለመወዳደር ጠይቆ ከፌዴሬሽኑ ይሁንታን በማግኘቱ በዚህኛው ውድድር ሳይካፈል ቀርቷል። በመሆኑም በመርሃግብሩ ተይዞ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡

በተመሳሳይ ዛሬም (ረቡዕ) በተያዘው መርሃግብር መሰረት ይደረጋሉ ተብሎ የተጠበቀው 2 ጨዋታዎች ቢሆኑም አንዱ ጨዋታ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ የዲቪዚዮኑን ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ያወጣው ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በዘንድሮው ውድድር የማናየው ቡድን ሆኗል፣ በዚህም ከቦሌ ጋር ሊያደርገው የነበረውን ጨዋታ ሳያከናውን ቀርቷል።

ዘንድሮ ቡድኑን አቋቁሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውድድር የገባው መቐለ 70 እንደርታ አዲስ አበባ ስቴዲየም ላይ በአቃቂ ክፍለ ከተማ 1ለ0 ተሸንፏል። ሃና ተስፋዬ በጨዋታው 36ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረችው ብቸኛ ግብ አቃቂን መክፈቻውን በሶስት ነጥብ እንዲያሳምር አድርጎታል።

Similar Posts