እግርኳስ

አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ድል ሲቀናት ንግድ ባንክም አሸንፏል

የ2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ፣ የአንደኛ ዲቪዚዮን ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርገዋል።

ከቀኑ 09፡00 ላይ በቀድሞዋ የድሬደዋ ወንዶች ቡድን አሰልጣኝ የሚመራው አዲስ አበባ ከተማ ጥረት ኮርፖሬትን አስተናግዶ 2ለ1 አሸንፏል። የአምናው የሁለተኛ ዲቪዚዮን ሻምፒዮን ጥረት ኮርፖሬት ግብ በማግባቱ በኩል ቀዳሚ ነበር።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ የጭማሪው ደቂቃ ላይ ሲደርሱ አዲስ አበባን አቻ የምታደርገዋን ግብ ፣ፍቅርተ ብርሃኑ አስቆጥራለች። ከምስር አብርሃም ጋር በመሆን የሁለተኛው ዲቪዚዮን ኮከብ ግብ አግቢ የነበረችው ፎዚያ መሀመድ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥራ አዲስ አበባ ከተማ ሶስት ነጥቡን እንዲያሳካ አስችላለች።

11፡00 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገናኘው ጨዋታ የተደረገ ሲሆን ንግድ ባንክ 2ለ1 አሸንፏል። ለአሸናፊው ቡድን አምበሏ ረሂማ ዘርጋ ሁለቱንም ግቦች አስቆጥራለች፣ መሳይ ተመስገን ደግሞ ለ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ብቸኛውን ግብ አስቆጥራለች፡፡

ይህ የአንደኛው ዲቪዚዮን ውድድር መክፈቻውን ያደረገው ዕሁድ በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ነበር። ሀዋሳ ከነማ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን 5ለ0 ሲያሸንፍ፣ አዳማ መከላከያን፣ ጌዲኦ ዲላ ድሬደዋን በተመሳሳይ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ሰኞ ህዳር 17 የሚደረግ የአንደኛው ሳምንት ቀሪ ጨዋታ ነው።

በሁለት ዲቪዚዮን ተከፍሎ የሚደረገው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር፣ የሁለተኛው ዲቪዚዮን ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ረቡዕ ይደረጋሉ።

Similar Posts