አትሌቲክስ

22ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

22ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ

መቼ – ጥቅምት 24/2011ዓ.ም, የት- ጊዮን ሆቴል

አመታዊው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጠቅላላ ጉባኤ የተለመደ እና የሚጥበቁ አጀንዳዎችን ያንሳ እንጂ በውይይቶች ወቅት በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል::

የጉባኤው 5 ነጥቦች

በጉባኤው የተነሱ አበይት ጉዳዮች
1. የአትሌቶች የምርጫ መስፈርት
ከአንድ አመት በላይ የአትሌቶች ማህበርን እና ፌደሬሽኑን ሲያወዛግብ የቆየው ይሄ ጉዳይ ነው::
በጉባኤው የስራ አስፈፃሚ አባል አትሌት ስለሺ ስህን “ይህ ጉዳይ መጨረሻ ይኑረው” በማለት በጉባኤው አምርሮ ሲናገር ተደምጧል:: ግልፅ ያለ የአትሌቶች ምርጫ መስፈርት ባለመኖሩ አትሌቶች ሆድ እና ጀርባ እየሆኑ ነው የሚሉት የአትሌቶች ተውካዮቹ ናቸው:: ኮማንደር ማርቆስ ገነቴ እና አትሌት የማነ ፀጋዬ ይሄንኑ ጉዳይ ጠንከር ባለ ድምፅ ተናግረዋል::
ከዚህ ጎን ለጎን አትሌቶች ልምምድ የሚሰሩበት በተለይም ለጎዳና ላይ ልምምዶች ይታሰብበት ብለዋል:: አትሌቶች በአስፋልት ከመኪና ጋር እየተጋፉ መሮጥ ይብቃቸው ብሔረሰቦችናማለት በአፅንኦት አስረድተዋል::

ለእነዚህ ጥያቄዎች የፌደሬሽኑ ምላሽ
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ

  • የምርጫ መስፈርቱን በተመለከተ በ15 ቀናት ውስጥ መልስ እንሰጣለን ብሏል:: ይሁን እንጂ መስፈርት ሊያስማማን አይችልም:: የሀገርን ውጤት ቅድሚያ እንስጥ ለዚህ ደግሞ የሁላችንም ሀላፊነት ነው በማለት አብራርቷል::
  • ማዘውተሪያ ቦታዎችን በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ በሰንዳፉ እና አዲስ አበባ ዙሪያ ስራዎችን ለመስራት እንዳቀዱ ይፋ አድርጏል::

ተ/ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደራቱ ቱሉ

  • አትሌቶችን በተመለከተ እኛም አትሌቶች ስለነበር ህመማቸው ይሰምናል:: እኛን ስለምን እንደውጭ ሰው ታዪናላችሁ ብላለች:: ረዝም ላሉ ደቂቃዎች ማብራሪያ የሰጠችው ደራርቱ አትሌቲክሱን ለማሳደግ የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል እዚህ ውስጥ አአትሌቲክሱን ለማሳደግ አንዱ ጠያቂ ሌላው ተጠያቂ ሊሆን አይገባም ስትል ከጉባኤተኛው የድጋፍ ጭብጨባ አግኝታለች:

ም/ፕሬዝዳንት ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም

  • ተቀራርቦ መስራት ያዋጣናል ብሏል::

2. የ2011ዓ.ም እቅድ በፌደሬሽኑ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ከቀረበ በሗላ ከተሳታፊዎች የተለያዪ ጥያቄዎች ተነስተዋል:: በተሳታፊዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ የተነሳበት የ2011 የውድድር ቦታዎችን በተመለከተ ነው:: በፌደሬሽኑ እቅድ መሰረት በአመቱ ብዙዎቹ ውድድሮች እቅድ የተያዘላቸው በአዲስ አበባ እንዲካሄዱ ነው::

ተሳታፊዎቹ

  • በክልል የተገነቡ ስታዲየሞች ምቹ በመሆናቸው እና ስታዲየሞቹም ያለውድድር ከሚዘጉ የውድድር እድል ይሰጣቸው
  • የአትሌቲክስ ውድድርን ለማስፉፉት ውድድሮች ወደ ክልል ይውጡ ብለዋል:

አቶ ቢልልኝ መቆያ ውድድሮች በአዲስ አበባ እንዲሆንየተፈለገው በበጀት እጥረት መሆኑን አስረድተዋል:: ይሁን እንጂ የፌደሬሽኑ ተ/ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደራቱ ቱሉ ኢትዮጵያ ሻምፒዮናን ጨምሮ ውድድሮች ወደ ክልል ቢወጡ ፍላጎቷ መሆኑን ገልፃ ስራ አስፈፃሚው ይነጋገርበታል ብላለች::

3. በ21ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ከአመት በፊት ተነስቶ መግባባት ላይ ባለመደረሱ በይደር የቆየው የክለቦች በጉባኤው የሚኖራቸው ተሳትፎ ይጨምር አይጨምር ውዝግብ በዚህም ጉባኤ እልባት አላገኘም::

በጉባኤው ሁለት ሀሳብ ሲነሳ ክለቦች የስፖርቱ መሰረቶች ናቸው ስለዚህ በዚህ ጉባኤው ድምፅ ይኑራቸው አንዱ ሀሳብ ሲሆን በዚህ ውሳኔ ብዙ ክለብ የሌላቸው ክልሎች ይጎዳሉ የሚለው ሌላው ሀሳብ ነው:: ፌደሬሽኑ ክለብ ለመባል የሚበቁ እና መስፈርቱን የሚያሟሉ አለመሆናቸውን አስረድቶ አሁንም ጉዳዪን በይደር አቆይቶታል::

4. መንግስት አሁንም ስፖርቱን በተለይም አትሌቲክሱን ልዩ ትኩረት እሰጠዋለሁ ብሏል::

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ድኤታ ሀብታሙ ሲሳይ ስፓርት መንግስት ትኩረት የሚሰጠው ዘርፍ ነው ብለዋል:: ለዚህም ሲባል ስፓርት ራሱን ችሎ በኮሚሽን ደረጃ መደራጀቱን ተናግረዋል:: አቶ ሀብታሙ አያይዘውም በአትሌቲክሱ በስፉት እየተውራ ያለው የተከለከሉ ሀይል ሰጭ ቅመሞች ጉባኤው አፅንኦት ይስጠው ብለዋል::

5. የአትሌቶች ፓስፖርት

በጉባኤው ላይ የተገኙት የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ተውካይ ዶ/ር ስቴፈን ቤርሞን አትሌቲክሰ ለኢትዮጵያ ከእግዚአብሄር የተሰጠ ሀብት ነው:: ይሄን ሀብት ማስተዋወቅ- መንከባከብ እና ማሳደግ ይኖርባችሗል ብለዋል:: በዚህ መሀል ግን የአትሌቶቻችሁ ፓስፓርት በተለያየ ጊዜ መቀያየር አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል:: ይህ ድርጊትም የእድሜ ማጭበርበር በመሆኑ ይታሰበት ብለዋል::
በእድሜ ጉዳይ ጉባኤውም ሀሳብ ተለዋውጧል:: የክልል ፌደሬሽኖች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንን ሲወቅስ ፌደሬሽኑ ክልሎች የሰጣችሁንን ነው ያሳተፍነው ብሏል::

አንድ ቀን የፈጀው 22ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ በመጨረሻ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማኑዋል በማስመረቅ ተጠናቋል::

የማሰልጠኛ ማኑዋሉን ይዘት በተመለከተ ሰፋ ያለ መረጃ በቅርቡይዘን እንመለሳለን::

Similar Posts