እግርኳስ

ደጋፊዎች ከክልል ወደ ክልል ሲዘዋወሩ መነሻቸውን ኢትዮጵያዊነት ማድረግ አለባቸው – ኢንጅነር ታከለ ኡማ

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የአዲስ አበባ ክተማ አስተዳደር በበጋራ ያዘጋጁት በከተማው ደረጃ ከሚገኙ የፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እና ብሔራዊ ሊግ ክለቦችና ደጋፊዎችን ያሳተፈ ውይይት በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ተካሄደ።

በመድረኩም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፣ ጀማሉ ጀምበር የአ.አ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የአ.አ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢ/ር ኃይለየሱስ ተገኝተዋል።

ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር የተጀመረ ሲሆን ምክትል ከንቲባው በጠየቁት መሰረት የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተቀላቅለው በመቀመጥ ፍቅራቸውን አሳይተዋል።

ደጋፊዎች ከክልል ወደ ክልል ሲዘዋወሩ መነሻቸውን ኢትዮጵያዊነት እንዲያደርጉ እና በአዲስ አበባ ደረጃ የሚተገበሩ መልካም ነገሮች ለሌላው ክልል ትልቅ አርአያ እንደሚሆን ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገልፀዋል።

በመድረኩ የተለያዩ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከተሰነዘሩት ሃሳቦች እና ከመድረኩ ከተሰጡ ምላሾች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው አሰናድተናቸዋል።

ቅዱስ ጊዩርጊስ ደጋፊዎች

 • የክለቦች ስታዲየም፣
 • የነጥብ ማጣት በተለይ ከጅማ ጋር በተደረገው ጨዋታ፣
 • የፀጥታ አስከባሪዎች ሁሉንም ደጋፊ እንደጥፋተኛ ማየት እና የስፓርቱን ባህሪ አለመረዳት፣
 • በሰታዲየም የመፀዳጃ ቤት ችግር (የሴት የወንድ)፣
 • የሚዲያ ወገኝተኝነት እና ተፅዕኖ፣
 • ሚድያዎች የሀገር ውስጥ ስፓርትን ትኩረት አለመስጠት፣
 • 80 ዓመት ሙሉ በታማኝነት ግብር የከፈለ ክለብ ሆኖ ሳለ ምንም እውቅና አልተሰጠውም፣
 • እንደዚህ አይነት ውይይቶች በየክልሉም መደረግ አለባቸው፣
 • የከተማ አስተዳደሩ ለጥቅም ብቻ አይፈልገን የሚሉት ይገኙበታል

ኢትዮጵያ ቡና

 • እግርኳሱ ከፖለቲካ እና ከዘር መፅዳት አለባቸው፣
 • ክለቦች አርማቸው ላይ ሳይቀር ብሔርተኝነትን እያንፀባረቁ ይገኛሉ፣
 • የኢ.እ.ፌ.የክለቦችን ገንዘብ በአግባቡ አይከፍልም ፣
 • የድጋፍ ማድመቂያዎችን ወደ ስታዲየም ይዞ መግባት አይቻልም፣
 • የፀጥታ አስከባሪዎች ከክለብ ወገንተኝነት መውጣት ይኖርባቸዋል፣
 • የሚዲያ አካላት ወገንተኝነት፣
 • በየመንገዱ ባክነው ያሉ ወንድሞቻችንን ወደ ስልጠና የሚያካትት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ፣
 • የክለብ ፀጥታ አስከባሪዎች (ስቴዋርዶች) ብዛት ከ100 እንዳይበልጡ የሚለው ውሳኔ አግባብነት የለውም፣
 • የተጫዋቾች ደሞዝ በወር መሆን አለበት የሚሉት ይገኙበታል

በተሰነዘሩት ሃሳቦች እና ጥያቄዎች ዙሪያ ባለድርሻ አካላቱ ምላሽ ሰጥተዋል
አቶ ኢሳያስ ጅራ፡- የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት

“በቅድሚያ እኛም የለውጡ ደጋፊ ነን፣ እግር ኳሱ ወደጎጥ ወርዷል አንሰን አንሰን ወርደናል፣ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ በእኛ ስብሰባ ብቻ ሳይሆን መንግስት ራሱ ከሚመለከታቸው ጋር ተወያይቶ ውድድሩ መደረግ አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን እንዲነግረን አቋም መያዝ አለብን፣

ትልቅ የመንግስት ትኩረት ያስፈልገናል አጋጣሚ ጠ/ሚኒስቴሩ ሀገር ውስጥ ስለሌሉ ከምክትሉ ጋር እናወራለን፣ እዚህ ስንናገር ጥሩ የምናወራ ግን ሜዳው ላይ ስንመጣ የምንቀየር አለን፣ አጀንዳ ይዘን ስለምንመጣ ነው ይሄን ሜዳ ስንመጣ መተው አለብን፣

እኛ የነውጠኝነታችን እና የረብሻው ደረጃ እላፊ እየሄደ ነው ዛሬ ሙስጠፋ መኪ ደም ወደ ውስጡ ፈሶበት መናገር አይችልም፣ ከዚህ ለመውጣት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን መሄድ አለብን ፣ ክለቦቻችንን ስንሰበስብ እውነት ውድድር አለ ብላችሁ ነው ወይ ነው የሚሉን፡፡

አሁን በአዲሱ ሪፎርም መሰረት የዲሲፒሊን መመሪያችንን አስተካክለናል ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት አለብን ብለን እየሰራን ነው፣ ለቅጣት በትር ብቻ የተዘጋጀንም አይደለንም እንደብሄራዊ ፌዴሬሽን በቅንነት ነው ማገልገል ያለብን፣ በጊዮርጊስ ደጋፊ ተመታሁ ብዬ ማቄም አልፈልፍም ስፖርት ውስጥ ነው ያደኩት ኢትዮጵያ ቡናም ሰደበኝ ብዬ ማቄም አልፈልግም የእኔ አጋጣሚ ሆኖ ከጅማ ሆነ እንጂ ይሄን ቦታ ከየትኛው የኢትዮጵያ ክፍል የመጣ ሰው ይመራዋል እንደዚህ ባይታሰብ ጥሩ ነው፡፡

በጨበጣ ነው የምታስተናግዱት የተባለው አዎ እውነት ነው 9.8 ሚሊየን ብር የክለቦች ዕዳ አለብን ይሄ የሆነ ቦታ መቆም አለበት አሁን የቡናን ከድሬደዋ ጋር ያለውን ነገ ገቢ ይደረጋል ሁለተኛው ጨዋታ ሳይጀመር ይገባል ብለን አስበናል የነበረውን ደግሞ ቀስ እያልን እንከፍላለን፡፡

የውጪ ተጫዋቾች ዙሪያ ላይ ብዥታ ስላለ ላጥራ በአንድ ሌሊት ይህን ነው ማለት አንችልም ተጫዋቾቹ ውል አላቸው ግን እየሄድንበት ነው፣ የታክስ ጉዳይ እኔም ጋር ራስምታቶች አሉ፣ አይደለም ግለሰብ የተቋምን ገቢ ማወቅ የሚያስቸግርበት ወቅት አለ ስለዚህ ሂደት ይፈልጋል፣ ይሰማል ግን ኮንክሪት የሆነ ነገር የለም እየተማማን ነው ስለዚህ ሌላውን ስንወነጅል የተጨበጠ ነገር መኖር አለበት፣ የተጫዋቾች ዝውውር ጉዳይ ግልፅነት ይፈልጋል” ብለዋል

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንይ

“በዚህ ውይይት ለእኛ እንደጥሩ ነጥቦች ያገኘናቸው ነገሮች አሉ፣ ስንነጋገር በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ፖሊስ አያስፈልግም ውድድሩ ሰላም ስለሆነ የፍርድ ቤት ሲሆን ወንጀለኛን ለማቅረብ ነው፣ ግን እዚህ አብሮ ሁከት የሚፈጥር ስላለ ነው የምንመጣው፣ በሜዳው ፖሊስ የሚገኘውም ለዛ ነው፣ በተጨባጭ ፖሊስ የሚመታበት የሚወረወርበት ጊዜም አለ ፣ እንደ ፖሊስ አመራር መቀበል ያለብን ነገር አለ፣ ፖሊስ የተለየ ነገር የለውም ሁከት ሲፈጠር ፖሊሳችን ያን ለይቶ የመስራት አሰራር ላይ ክፍተት አለበት፣ ስህተቱን ግን እያየን እያረምን ፖሊሳችንን ማብቃት ግዴታ ነው፣ አመራራችን ዝግጁ መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁ፣ ፖሊስ የማንም ደጋፊ መሆን የለበትም ዋና ግቡ እዛ አካባቢ ሰላም ማስከበር ብቻ ነው፣ ከእናንተው ጋር ሆነን እንሰራለን ፣ በከፍተኛ ደረጃ ተቀራርበን እንሰራለን፣ ስፖርታችን ስፖርታዊ ውድድር ብቻ እንፈልጋለን፣ ስፖርታችን ዘር እና መሰል ነገር የማይንፃባረቅበት መሆን አለበት” ብለዋል

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካይ

“ከደጋፊዎች ጋር በጋራ ሰርተን ለውጥ የመጣንባቸው ነገሮች አሉ፣ ያዳላሉ የተባሉ አባላት ካሉን እናስተካክላለን እናርማለን፣ ድብደባ የተባለው አዎ አለ ግን ነገሮች ሲደፈርሱ እና ከአቅም በላይ ሲሆኑ ነው፣ ከአቅም በላይ የሆኑብን ነገሮች አሉ፣ የእኛም አባሎች ጥያቄ ያነሳሉ እኛም ውስጣችንን ማየት አለብን እንደምንናገረው አይደለም፣ ሁላችንም አንድ ሆነን የምንሰራበት መንገድ መፈጠር አለበት፣ ስፖርታዊ ጨዋነቱ ከአቅም በላይ ነው የሆነብን ፣ ታዛዥ የማይሆን አለ የህግ የበላይነቱም ይታሰብበት በአጠቃላይ የተቀመጡ ነገሮችን ወስደን እንሰራበታለን ። ” ብለዋል

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ

“የሁላችሁንም ጥያቄ ይዘናል፣ የተሰራው አልተሰራም ሳንል ግን የበለጠ መስራት እንዳለብን አስባለሁ፣ የስፖርቱን ጤናማነት በማሰብ ሁሉም የየራሱን ስራ ይስራ፣ ስፖርት ከብሄር እና ከቋንቋም በላይ ነው ወደብሄር፣ ወደቋንቋ እና ግለሰብ ስናወርደው አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ወደዛ እንዳናወርደው ማሰብ ይገባናል፣ እንደእኔ እንደግለሰብ ሆኜ ከክልል ከንቲባዎች ጋር አወራለሁ፣ ከዚህ የሚበልጥ ከዚህ የተሻለ ስራ ስለሌለ በጋራ እንሰራለን።

መንግስትም እንደ መንግስት ጋዜጠኛም እንደ ጋዜጠኛም ሚናን መውጣት ያስፈልጋል ሙያ እና ግላዊ ስራ መለየት አለበት እኔም እሰማለሁ የስፖርት ፕሮግራሞች ኔጌቲቭ ፓርቱን ብቻ አትዩ ጥሩውንም እዩ በዚህ ደረጃ ሁሉም የራሱን ስራ እንዲሰራ እርግጠኛ ነኝ የተሻለ ነገር መስራት ይችላል፣ ጋዜጠኞቻችንም ሲጨንቃቸው ይመስለኛል የአውሮፓውን የሚያበዙት የተመቻቸ ነገርም የላቸውም ኢትዮጵያን የምንወድ ከሆነ ከነበረችባት ማማ እንድትመለስ የምንፈልግ ከሆነ መጀመሪያ ከራሳችን እንጀምር፣ ሀላፊነታችንን የራሳችንን ቆጥረን እንቀበል፣ ፌዴሬሽንም ሀላፊነት አለበት፣ ሁሉም እንደዛው ይሄ ርስት አይደለም ነገም ሌላ ሰው ይመጣል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተነሳው ነጥብ የግብር የተሸለመው ትንንሽ የከፈሉት ናቸው እናንተ ከፍተኛውን ከፍላቹሃል ያኔ ከከፍተኞቹ ጋር ትሸለማላችሁ፣ ኢንዱስትሪው መታወቅ አለበት፣ ዜጎች እንደዜጋ ማሰብ አለብን፣ ሜዳዎችን መልስ አልሰጥም ቁጭ ብለን የቱ ዝግ ነው የቱ አለ የሚለውን እንሰራለን፣ የተዘጉ እንዲከፈቱ እናደርጋለን፣ ግን ደግሞ ባለሀብቶቹን ላንጫን እንችላለን፣ የስፖርት ተቋማቱ ከእናንተ ጋር እንዲሰሩ እናደርጋለን፣ ማስ ስፖርት ያስፈልጋል እሱ ነው የሚያስፈልገን፣ መከፈት ያለበትን ሜዳ እንከፍታለን በፌዴራል ደረጃ የተያዙም ካሉ አነጋግረን እናስከፍታለን የወጣቶቹ ነው መሆን ያለበት፣ ስለከፍታ ላውራችሁ ሁላችንም ያለንንበትን ከፍታ ማወቅ አለብን፣ አንድ ፕሌን ከተፈቀደለት ውጪ ሲበር የሚሆነውን ማሰብ ነው፣ ይሄን ኢንደስትሪ ወደ ከፍታ መመለስ አለበት፣ እንደሀገር ለውጥ ያስፈልጋል እግር ኳስም ለውጥ ይፈልጋል፣ የፕሮፌሽናሊዝምን ፅንሰሀሳብን ይዘን መጓዝ አለብን።” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል

Similar Posts